Thursday, April 26, 2018
Home Blog

ካንዬ ትራምፕን በትዊተር በመደገፉ ዘለፋን እያስተናገደ ነው

0

አሜሪካዊውው ታዋቂ የሂፕ ሆፕ አቀንቃኝ ካንዬ ዌስት በቅርቡ በትዊተር ገፁ ለፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ድጋፍ መስጠቱን ተከትሎ ብዙዎች ወቀሳቸውን እየሰነዘሩ ነው።

የ40 ዓመት እድሜ ያለው ካንዬ ትራምፕን በሚደግፉ በተከታታይ በትዊተር ካሰፈራቸው ፅሁፎቹ መካከል “አሜሪካን እንደገና ታላቅ ማድረግ” የሚለውን የፕሬዚዳንቱን መፈክርና በትራምፕ የተፈረመበት ቀይ ኮፍያም አጥልቆ ታይቷል።

“ከትራምፕ ጋር መስማማት ማንም አይጠበቅበትም ነገር ግን፤ የህዝቡ ግፊት ግን ትራምፕን ሊያስጠላኝ አይችልም” በማለት በትዊተር ገፁ አስፍሯል።

ትራምፕ በአፀፋ ምላሻቸው በትዊተር ላይ “ካንዬ አመሰግናለሁ! አሪፍ ነው” ብለዋል።

ካንዬ በተለያዩ ድረ-ገፆች ዘለፋን ማስተናገዱን ተከትሎም ባለቤቱ ኪም ካርዳሽያን ዌስት በበኩሏ ደግፋው ተከራክራለች።

“ባለቤቴን ጥላሸት ለመቀባት ለምትጣጣሩ የሚዲያ አካላት በሙሉ ካንዬ ቀውሷል እንዲሁም በትዊተር ገፁ ያሰፈረው ይረብሻል የሚለው አስተያየታችሁ አስፈሪ ነው።

ሀሳቡን በነፃነት ስለገለፀና ራሱን ስለሆነ የአዕምሮ ጤንነት መጓደል ነው ብላችሁ ለመፈረጅ ወይ ፍጥነታችሁ! ትክክል አይደለም” ብላለች።

ካንዬና ትራምፕ የተዋወቁት ፕሬዚዳንታዊ ምርጫውን ካሸነፉ በኋላ ሲሆን ባለፈው ረቡዕም ከትራምፕ ጋር “የድራጎንን ኃይል እንደሚጋሩ” እንዲሁም ትራምፕ “ወንድሙ እንደሆኑ” በትዊተር ገፁ ላይ አስፍሯል።

ካንዬ ቺካጎ ያደጉትን የቀድሞ ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ ባለፉት ስምንት ዓመት ስልጣን ላይ ቢቆዩም “ችካጎ ምንም አልተቀየረችም” በሚል ተችቷቸዋል።

አስተያየቱም የትዊተር ድረ-ገፅ ተጠቃሚዎችን ያበሳጨ ሲሆን አንድ የትዊተር ተጠቃሚም የዘፋኙን “ዘ ላይፍ ኦፍ ፓውሎ” የሚለውን ዘፈኑን በመጥቀስ “የዱሮው ካንዬ ናፈቀኝ” ብላለች።

ኪም ካርዳሽያን ትችቶቹን በማጣጣል” ካንዬ በመንጋዎች የሚንሸራሸር ሀሳብ አይደግፍም ለዚህም ነው የምወደው እንዲሁም የማከብረው።

ከጥቂት ዓመታት በኋላ እንደሱ አይነት ተመሳሳይ አስተያየት የሚሰጡ እንደሱ አይፈረጁም እንዲያውም ይመሰገናሉ።

ካንዬ ከጊዜው የቀደመ ነው” ብላለች።

ከእሷም በተጨማሪ ቻንስ ተብሎ የሚታወቀው ራፐርም በትዊተር ላይ ባሰፈረው ምላሽ የአዕምሮም ሆነ አካላዊ ጤንነቱን ለሚጠራጠሩት “በደህና ሁኔታ ላይ ነው ያለው” በማለት የድጋፍ ምላሽ ሰጥቷል።

ካንዬም በበኩሉ ከባለቤቱ ምክር በመስማት የሚስማማው ከራሱ ጋር ብቻ እንደሆነ ምላሽ ሰጥቷል።

አስተያየትዎን ይፃፉ

ለሽያጭ የሚያዘጋጅ ‘የህፃናት ፋብሪካ’ በናይጄሪያ

0

አንድ መቶ ስድሳ ሁለት ልጆች “የህፃናት ፋብሪካ” ተብለው በሚጠሩ ወላጆቻቸውን ያጡ የህፃናት ማቆያዎች ውስጥ መገኘታቸውን የናይጄሪያ መገናኛ ብዙሃን ዘገቡ።

እነዚህ የህፃናት ፋብሪካ ተብለው የሚታወቁት ስፍራዎች ትክክለኛ ተግባር ምን እንደሆነ በግልፅ የሚታወቅ ነገር የለም።

ይህ ስያሜ አንዳንድ ጊዜ የተጣሉ ወይም ወላጆቻቸውን ያጡ ህፃናት የሚቆዩባቸው ቦታዎች ከመሆናቸው ባሻገር ህፃናቱ ለትርፍ የሚሸጡባቸው እንደሆነም ይነገራል።

ነገር ግን ቀደም ብሎ አጋጥሞ በነበረ ክስተት “የህፃናት ፋብሪካ” የሚለው ስያሜ ነፍሰ-ጡር ሴቶች እስኪወልዱ ድረስ የሚቆዩበትና ከወለዱ በኋላም ልጆቻቸው የሚሸጡበት ቦታ ነው።

ትናንት 162 የሚደርሱት ሕፃናት ከተገኙ በኋላ የሌጎስ ግዛት ወጣቶችና ማህበራዊ ልማት ሃላፊ የሆኑት አግቡላ ዳቢሪ ሲናገሩ “የህፃናቱን ደህንነት ለማረጋገጥ ወላጆቻቸውን ያጡ ህፃናት የሚቆዩባቸውን ሦስት ማዕከላትን መዝጋት አለብን። ከእነዚህ መካከልም አንዱ የህፃናት ፋብሪካ የሚባል ሲሆን ሁለቱ ያለተመዘገቡ ሕገ-ወጦች ናቸው” ብለዋል።

ሃላፊው ጨምረውም በእነዚህ የህፃናት ፋብሪካዎች ውስጥ የተገኙት ልጆች መንግሥት እውቅና በሰጣቸው ማቆያዎች ውስጥ እንክብካቤና ጥበቃ እየተደረገላቸው መሆኑንም ተናግረዋል።

አስተያየትዎን ይፃፉ

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ በሀዋሳ ስታዲየም ያደረጉት ንግግር

0

የተከበራችሁ የመንግስት ከፍተኛ አመራሮች፤
የሀይማኖት አባቶችና የሀገር ሽማግሌዎች፤
የሀዋሳ እና አካባቢዋ ነዋሪዎች ክቡራትና ክቡራን፤
ታቦር ተራራን ከራስጌ፣ የሀዋሳ ሀይቅን በግርጌ አድርጋ ከዕድሜዋ በላይ በፈጣን የእድገት ግስጋሴ ላይ በምትገኘው የክልሉ መዲና በሆነችው በውቢቷና የፍቅር ከተማ ሀዋሳ እና በእንግዳ ተቀባይ ሕዝቦቿ መሀል በመገኘቴ የተሰማኝን ልባዊ ደስታና ክብር ለመግለጽ እወዳለሁ፡፡

የደቡብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ኢትዮጵያዊነት በህብረ ብሔራዊ ቀለማት ያጌጡ የአንድነትና የአብሮነት ረቂቅ ሸማ ድርና ማግ ሆኖ የተወዳጀበት የታላቋ የኢትዮጵያ ነጸብራቅ ትንሿ ኢትዮጵያ ናት፡፡ የዚህ ክልል ህዝብ እንደ ሌሎች የኢትዮጵያ ህዝቦች ሁሉ የረጅም ዘመን ታሪክ እና የጥንታዊ ስልጣኔ ባለቤት ነው፡፡

ከአራት ሺህ አመታት በላይ የዘለቀ እንሰትን ጨምሮ የሠብል ልማት እርሻ፣ የሥነ ጥበብና እደጥበብ ሙያ፣ የተለየ የዘመን አቆጣጠር፣ የተደራጀ ጥንታዊ አስተዳደርና ፖለቲካ ሥርዓት ባለቤት የሆኑ ህዝቦች ያሉበት ክልል ነው፡፡

ክቡራትና ክቡራን፤
የደቡብ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ትናንትም፣ ዛሬም ኢትዮጵያ ነፃነቷንና አንድነቷን ጠብቃ እንድትኖር ከተቀረው የሀገራችን ሕዝብ ጋር በአብሮነት በመሰለፍ በተለያዩ የጦር ግንባሮች ታላቅ ጀግንነት የፈፀም ህዝብ ነው፡፡
የክልሉ ሕዝብ በቀጣይነትም ኢትዮጵያ ሉላዊንቷን ጠብቃ እንድትቀጥል በከፍተኛ የአርበኝነትና የሀገር ፍቅር ስሜት የድርሻውን በመወጣት ለሀገራችን ህልውና አለኝታ እንደሚሆን ፅኑ እምነት አለኝ፡፡
ይህ ህዝብ በሠላም ለመጡበት ሁሉ እጁን ዘርግቶ ፣ያለውን አካፍሎ፣ መኝታውን ለቆ በአብሮነት ለመኖር ከፊት ተርታ የሚሰለፍ ነው፡፡

በሀገር ባለቤትና በማንነታቸው ኮርተው ከሌሎች የሀገራችን ህዝቦች ጋር በወንድማማችነት በጋራ ለመኖር ለዘመናት ያካሄዱት የአርበኝነት ተጋድሎ እና የተከፈለው መስዋዕትነት የምንዘክረው ብቻ ሳይሆን ዘብ የምንቆምለት አላማ ነው፡፡

የሲዳማ፣ ወላይታ፣ ጉራጌ፣ ቀቤና፣ ሀዲያ፣ ማረቆ፣ ስልጤ፣ ጌዴኦ፣ ዳውሮ፣ ጋሞ፣ጎፋ ፣ የም፣ አይዳ፣ ባስኬቶ፣ ከምባታ፣ ሀላባ፣ ጠምባሮ፣ ዶንጋ፣ ቡርጂ፣ ኮንሶ፣ ደራሼ እና ኮሬ ህዝቦች ያደረጉትን የሞት ሽረት ትግልን በማስታወስ የሚያበቃ ሳይሆን የካፋ፣ ቤንች፣ ሸካ ፣መኢኒት እና የደቡብ ኦሞ ህዝቦች እስከ አድዋ ጦርነት መባቻ ድረስ ገባርነትን መከላከል ችለው እንደነበር ታሪክ የሚዘከረው ነው፡፡

ክቡራትና ክቡራን፤
ይህ ክልል በልዩነት ውስጥ አብሮ መኖር አንደሚቻል ያስመሰከረና አርዓያ መሆን የሚችል ነው፡፡

በልዩነት ውስጥ ጠንካራና ፅኑ የሆነ አንድነትና ያለው፣ አንዲሁም ግሩም የሆኑ የጋራ እሴቶች ባለቤት የሆነ ህዝብ መኖሪያ ክልል ነው፡፡

የደቡብ ኢትዮጵያ ህዝቦች የየራሳቸው ቋንቋ፣ ባህልና ታሪክ ያላቸው መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ ለአብነት ያክል በባህላዊ የቤት አሰራር፣ የእንሰት አመራረትና ዝግጅት ፣ በህዝባዊ በዓላት አከባበር እንዲሁም በሀገር በቀል እውቀቶች አጠቃቀም እና በመሳሰሉት ለበርካታ ዘመናት የዘለቀው ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ግንኙነቶች የክልሉን ህዝብ የሚያስተሳስሩ የጋራ እሴቶች ፈጥረዋል፡፡

የክልሉ ህዝብ ለረጅም ዘመናት ሲተዳደርባቸዉ የነበሩ የየራሱ የተደራጀ ጥንታዊ የአስተዳደርና የፖለቲካ ስርዓት ያላዉ ብቻ ሳይሆን የራሱን መሪ የሚሰየምበት የስልጣን ርክክብ የሚያከናወንበት፣ የሀሳብ ልዩነቶችን የሚያስተናግድበት ፣ ግጭቶችን በሰላማዊ መንገድ የሚፈታበት፣ በቋንቋው የሚዳኝበት፣ ማንነቱን የሚገልጽበት፣ የጀግንነት ተግባር የፈጸሙትን የሚበረታታበትና የሚሸልምበት የዳበረ ጥንታዊ ባህላዊ የአስተዳዳር ስርኣት ባለቤት መሆኑን ታሪክ ብቻ ሳይሆን ዛሬም የሚታይ እውነታ ነው፡፡

በመሆኑም አልፎ አልፎ በራሱ ዉስጥም ሆነ ከአጎራባች ወንድሞቹ ጋር የሚከሰቱ ለህይወትና ንብረት ውድመት ምክንያት የሆኑ ግጭቶችን በማስወገድ፣ ጥንታዊ ባሕላዊ ስርዓቱን በማጠናከርና በመጠቀም ህብረ ብሔራዊ አንድነታችን ለማስቀጠል የበኩሉን አስተዋፅኦ እንደሚያደርግ አልጠራጠርም፡፡

በዚህም ረገድ የፌዴራል መንግስት ከክልሉ መንግስት ጋር በመሆን አበክሮ የሚሰራ መሆኑን በዚሁ አጋጣሚ ልገልፅላችሁ እወዳለሁ፡፡

ክቡራንና ክቡራን፤

ክልሉ በአመዛኙ የመሬት ጥበትና ከፍተኛ የህዝብ ቁጥር መጨመር ከሚስተዋልባቸው የሀገራችን ክፍሎች መካከል አንዱ በመሆኑ በክልሉ የተመዘገበው ፈጣን እድገት የሁሉንም የክልሉን ነዋሪዎች ተጠቃሚነት ማረጋገጥ እንዳላስቻለ ከህዝቡ የዕለት ተለት ኑሮ የምንረዳው ነው፡፡

በጤና ፣ በትምህርት፣ በመንገድ፣ በመብራት፣ በውሃ እና ሌሎች መሰረተ ልማቶች ለማደረስ የተደረገው እንቅስቃሴ ረጅም ርቀት መጓዙ የሚካድ ባይሆንም ከህዝቡ ፍላጎት አንፃር ግን ገና ብዙ መስራትን የሚጠይቅ ሠፊ ክፍተቶች ያሉበት መሆኑ ሀቅ ነው፡፡

ይህን እውነታ ለመለወጥ የፌዴራል መንግስት ከክልሉ መንግስት ጋር በመሆን በየትኛውም ደረጃ ስራ ሳይንቁ ሰርተው ለመለወጥ ደፋ ቀና የሚሉ የክልሉን ሕዝቦች ከጎናችን በማሰለፍ በአጠቃላይ የክልሉን ሕዝብ ሕይወት በተለይም የወጣቱን ሕይወት የተሻለ ለማድረግ በትጋት እንሰራለን፡፡

እዚህ ላይ ግን ልብ ልንለው የሚገባ ጉዳይ “ወንዝ ዳር ቆማ የምትጠጣው ውሃ ከሠማይ እስኪዘንብ እንደምትጠብቅ ወፍ” እግርና እጃችንን አሳስረን መቀመጥ አይኖርብንም፡፡

የደቡብ ክልል ሕዝቦች ታታሪ ሠራተኛነት እና ድንቅ የመቆጠብና የመሻሻል መንፈስ ከራሳቸው አልፎ ለበርካታ ኢትዮጵያውያን አብነታዊ ተምሳሌት ናቸው፡፡

ይህ ሕዝብ ጠንክሮ የመስራትን ብቻ ሳይሆን የመተባበርና መደጋገፍን ዋጋ አስቀድሞ በመረዳት ባንክ ሳይፈጠር፣ አክሲዮን ሳይመጣ ፣ሴፍቲ ኔት ሳይቋቋም በፊት ባህላዊ የእቁብና የእድር ስርዓትን የመሰረተ ለተቀረው የሀገራችን ሕዝቦችም ያሸጋገረ ሕዝብ ነው፡፡

በዚሁ ባህላዊ ሥርኣት ትናንት አያሌ የክልሉ እና የሀገራችን ሕዝቦች ችግርን ማሸነፍ እንደቻሉት ሁሉ የዛሬውም ትውልድ የአባት አያቶቹን ታታሪ ሠራተኛነት እና ድንቅ የመቆጠብና የመሻሻል መንፈስ ከመተባበርና መደጋገፍ ስርዓቱ ጋር በማስተሳሰር ለራስ፣ለቤተሰብ፣ለክልልና ሀገራዊ እድገት የልማት አርበኛ እንዲሆን በዚህ አጋጣሚ ጥሪዬን አቀርባለሁ፡፡

ከዚህ ቀደም በውጭ ሀገር ሰዎች የተያዙ የንግድ ስራዎችን በሀገር ዜጎች መተካት ሀገርን ፣ ከእጅ መጠምዘዝ የታደጉ በቤተሰብ የሚመራ ንግድ በኢትዮጵያ ያስተዋወቁ ቀደምት የልማት አርበኞች እንደነበሩ ፣ የዛሬዎቹ የእዚህ ክልል ህዝቦች በመረዳት መታወቂያችሁ የሆነውን ታታሪ ሠራተኝነትና ሀገር ወዳድነት በውስጣችሁ ሕያው መንፈስና የጉዞ አቅጣጫ ጠቋሚ ኮምፓስ በማድረግ ለሀገራችሁ ሠላም፣ ዴሞክራሲና ልማት ዘብ በመቆም ታሪክ ትሰሩ ዘንድ ጥሪዬን አስተላልፋለሁ፡፡

ውድ የደቡብ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች

ይህ ክልል በመንደር፣ በአካባቢ ያልታጠረ አድማስ ተሻጋሪ አብሮ የመኖር ባህል ያለዉ ብቻ ሳይሆን ፣በግለሰብና ማህበረሰብ መካከል ተፈጥሯዊ ሚዛን ተጠብቆ የሚኖርበትን ሀገር በቀል የግብርና፣ የተፈጥሮ ጥበቃ የህግና የአስተዳደር ሥርዓት ዛሬም ድረስ ማዝለቅ የቻለ ነዉ፡፡

በዚሁ ክልል የስምጥ ሸለቆ ትሩፋት የሆኑ የተለያዩ የውሀ ሀብቶች ለአብነት ያህል አባያ፣ ጫሞ፣ ሐዋሳ፣ የሩዶልፍ ሀይቆች፣ ኦሞ ወንዝ እና ሌሎችም የሚገኙበት ከመሆኑ በተጨማሪ ክልሉ በአለም አቀፍ ደረጃ እውቅና ያገኙ የሚዳሰሱና የማይዳሰሱ ቅርሶች ለአብነት ያህልም የኮንሶ እርከን ስራ፣ ጢያ ትክል ድንጋይ፣ የካፋ የጫካ ቡና፣ የሲዳማ ፍቼ ዘመን መለወጫ፣ የታችኛው ኦሞ ሸለቆ መካነ ቅርስ፣ የጌዴኦ ጥምር ግብርና ተጠቃሽ ሀብቶች ናቸው፡፡

እነዚህ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ፋይዳ ያላቸው ሀብቶች የክልሉን ህዝቦች ተጠቃሚነት ማሳደግ ለሚችል ልማት መነሻ ብቻ ሳይሆኑ ደቡብንም የኢትዮጵያ እስትንፋስ የማድረግ አቅም የታደሉ ናቸዉ፡፡

በመጨረሻም በተለመደው የእንግዳ ተቀባይነት ባህሉ ፣ ዳኤ ቡሾ፣ በላለዲ ይምጣ ፣በአፈር ንተን፣አሻም በማለት በፍፁም ፍቅር እጆቹን ዘርግቶ ለተቀበለን ሕዝብና ለክልሉ አመራሮች እኔም ከወገቤ ዝቅ በማለት ምስጋናዬን አቀርባለሁ፡፡

ኢትዮጵያ በልጆችዋ ጥረት ታፍራ፣ ተከብራና በልፅጋ ለዘላለም ትኑር!
ፈጣሪ ኢትዮጵያንና ልጆቿን ይባርክ
አመሰግናለሁ!

አስተያየትዎን ይፃፉ

ቡግር (ቡግንጅ) (PIMPLES)

0

እስከዛሬ ድረስ በህይወትዎ ዘመን በፊት ገጽ ቆዳዋ ላይ ወይም በሌላ ሰዉ ፊት ገጽ ቆዳ ላይ በመጠኑ አናሳ የሆነ ጠንከር እና ቀላ ያለ ጉብታ ተመልክተዉ ያዉቃሉ?

እናም በምን ምክንያት ሊከሰት እንደሚችል እንዴትም ማስወገድ እንደሚቻል ጥያቄ ሆኖቦት ያዉቃልን?

እንግዲያዉስ ዋናዉ ጤና ነዉ እና ፤ይህ አምድ እነዚህን ጥያቄዎች ከጤንነታችን አንጻር በጥልቀት በመቃኘት ለመመለስ ይሞክራል፡፡ ይህ ቀላ ያለ ጉብታ በህክምናዉ አጠራር ቡግንጅ ይባለል፡፡

ቡግንጅ መጠኑ የበዛ የሰዉነት ፈሳሽ ዘይት በቆዳችን ላይ የሚገኙ ትንንሽ ቀዳዶች ዉስጥ ታፍኖ ሲቀር የሚፈጠር ክስተት ነዉ፡፡

በቆዳችን ላይ የሚገኙ ትንንሽ ቀዳዶች ዉስጥ ሴባሺየስ እጢዋች የሚገኙ ሲሆን የሰዉነት ፈሳሽ ዘይትን ያመነጫሉ፡፡

የላይኛዉ የቆዳችን ክፍል ሁልጊዜም ያለማቋረጥ እራሱን ያድሳል፤ይህንንም በሚያደረግበት ጊዜ ሳይለወጡ የቀሩ የሞቱ የቆዳ ሴሎች እርስበራሳቸዉ በሰዉነት ፈሳሽ ዘይት አማካኝነት ሊያያዙ ይችላሉ፡፡

ይህም ክስተት በቆዳችን ላይ የሚገኙ ትንንሽ ቀዳዶችን እንዲደፈኑ ያደርጋቸዋል፤በተለይም በጉርምስና ወቅት ቆዳችን እየወፈረ ስለሚመጣ ክስተቱን ያበዛዋል፡የሴባሺየስ እጢዋችም መጠኑ ከፍ ያለ የሰዉነት ፈሳሽ ዘይትን ማመንጨትን ይጀምራሉ ይህም የሚሆነዉ እርስበራሳቸዉ ከተያያዙት ቆዳዋች ጀርባ ነዉ፡፡

የተጠራቀመዉ የሰዉነት ፈሳሽ ዘይት ለተለያዩ ባክቴሪያዎች በተለይም ፕሮፒኖባክቴሪየም አክኔ ዝርያ የሆነዉና ኢንፌክሽን እና ማቃጠልን ለሚያስከትለዉ ባክቴሪያ መሸሸጊያን ይፈጥራል፡፡

በዛ ያሉ ቀይ ቡግንጆች በተቃጠለ ሴባሺየስ እጢ ምክንያት ሲከሰቱ ቡግር በመባል ይጠራሉ፡፡

ስለ ሚከሰቱበት ሁኔታ ይህን ያህል ካልን እስኪ ደግሞ አይነታቸዉን ለማየት እንሞክር፤የተለያዩ የቡግንጅ አይነቶች አሉ ሆኖም ሁሉም አጀማመራቸዉ ከቆዳችን በላይ በሚያብጥ የቆዳ ቀዳዳ ነዉ፡፡

መልካቸዉን እና መጠናቸዉን በመመርኮዝ እንደሚከተለዉ ልንለያቸዉ እንችላለን፡፡

ጥቁር ራስ ያለዉ እና ነጭ እራስ ያለዉ

ትንንሽ የቆዳ ቀዳዶች በዘይት፣በሞተ ቆዳ እና በባክቴሪያ ምክንያት ሲደፈኑ ጥቁር ራስ ወይም ነጭ ራስ ያላቸዉ ትንንሽ ጉብታዋች በቆዳችን ላይ መታየት ይጀምራሉ፡፡

የተደፈነዉ ቆዳ ከአናቱ ላይ ክፍት ሲሆን ጠቋራ መልክ ይይዛል እናም ጥቁር እራስ ያለዉ ቡግንጅ ብለን እንጠራዋለን፡፡

የተደፈነዉ ቆዳ ከአናቱ ላይ የተደፈነ ሲሆን የጉብታዉ መልክ ወደ ነጭ ይጠጋል እናም ነጭ ራስ ያለዉ ቡግንጅ እንለዋለን፡፡

ፓፑለስ እና ፑስቱለስ

አንዳንድ ጊዜ የተደፈኑት የቆዳ ቀዳዶች ከሚጠበቀዉ በላይ በመቃጠላቸዉ ምክንያት ይቆጣሉ፤ይህም ሲሆን የቆዳችን ቀዳዶች ግድግዳ ይፈርሳል፡፡

ይህም ክስተት መጠናቸዉ ከፍ ያለ ፓፑለስ እና ፑስቱለስ የተባሉ ቡግንጆችን ይፈጥራል፡፡

ፑስቱለሶች ልክ እንደ ፓፑለሶች ናቸዉ፤ሆኖም ግን መልካቸዉ ቢጫማ ሲሆኑ የሞቱ ነጭ የደም ሴሎችን የያዘ ፈሳሽ ይሞላቸዋል፡፡

ኖዱልስ እና ሲይስትስ

የቆዳ ቀዳዶች ከመጠን በላይ በመቃጠላቸዉ ምክንያት ሲቆጡ መጠናቸዉም በዛዉ ልክ ይጨምራል፡፡

እንዲያዉም ወደ ቆዳችን ዉስጥ ጠልቀዉ ይገባሉ፡፡ይህም ከፍ ያለ የህመም ስሜትን ይፈጥርብናል፡፡

ኖዱልስ ጠንከር ያሉ ናቸዉ፡፡ሲይስትስ በበኩላቸዉ የሞቱ ነጭ የደም ሴሎችን የያዘ ፈሳሽ ስለሚሞላቸዉ ለስለስ ይላሉ፡፡

በነገራችን ላይ እርስዎ ወይም የሚያዉቁት ሰዉ የኖዱልስ እና ሲይስትስ ቡግንጆች በቆዳ ላይ ከተከሰቱ የህክምና ባለሙያን ማማከር አስፈላጊ ነዉ፡፡

ቡግንጅን ያመጣል ተብሎ የሚታመን የታወቀ ነጠላ መንሰኤ የለም፡

፡ምንም እንኩዋን በተለምዶአዊ ግምት ዘር፣የአመጋገብ ስነስርአት፣ቆሻሻ እና ጭንቀት ቡግንጅን ያስከትላል ተብለዉ ቢታሰቡም በቡግንጅ አመጣጥ ላይ ምንም ሚና የላቸዉም፡፡

በአንዳንድ የቡግንጁ ተጠቂዋች ላይ የሚከተሉት መንስኤዋች አስተዋጾ ያደርጋሉ፡፡

ቆዳ ላይ የሚያርፍ ዉጥረት ፡ በአንዳንድ ታማሚዎች ላይ ከአደጋ መከላከያ ቆብ ፣ከአገጭ መደገፊያዎች እና ከኮሌታ የሚመጣ ዉጥረት ቡግር(ብዛት ያላቸዉ ቡግንጆች) መከሰትን ያባብሳሉ፡፡

መድሃኒት ኪኒኖች ፡ አንዳንድ የህክምና መድሀኒቶች ቡግር(ብዛት ያላቸዉ ቡግንጆች) እንዲከሰትና እንዲባባስ ያደርጋሉ፡፡

ከመድሀኒት ኪኒኖቹም ምሳሌ ለመስጠት ያክል አዮዳይድ የያዙ መድሃኒቶች፣ብሮማይዶች፣በአፍ ወይም በሲሪንጅ የሚሰጡ አትሌቶችና ሰዉነት ገንቢ ስፓርተኞች የሚወስዱዋቸዉ አነቃቂ መድሃኒቶች መጥቀስ ይቻላል፡፡

የመተዳደሪያ ስራ ሁኔታ ፡ በአንዳንድ የስራ ዘርፎች ለኢንደሰትሪያል ምርቶች ተጋላጭ የምንሆንበት ሁኔታ ብጉርን ያስከትላል፡፡ለዚህም እንደምሳሌ ለመቅሮጫ የምንጠቀምባቸዉ ዘይቶችን መጥቀስ ይቻላል፡፡

ኮስሞቲክሶች ፡ አንዳንድ ኮስሞቲክሶችና የቆዳ መጠበቂያ ምርቶች የቆዳ ቀዳዶችን ይደፍናሉ፡፡

በዚህም ባህሪያቸዉ ምክንያት “ ኮሜዶጄኒክ “ ተብለዎ ይጠራሉ፡፡

የኮስሞቲክሰ ምርቶችን ልንሸምት ስንፈልግ የኮስሞቲክስ ምርቱ በዉስጡ የያዘዉን ንጥረነገሮች አንብበን ዉሀ በዝርዝሩ ላይ በመጀመሪያ ወይም በሁለተኛነት መጠቀሱን አጢነን መግዛት ብጉር እንዳይከሰትብን በምናደርገዉ ጥንቃቄ ላይ ትልቅ ጠቀሜታ አለዉ፡፡

ከእነዚህ “ ዉሃ በዉሰጣቸዉ የያዙ“ የኮስሞቲክስ ምርቶች መካከል አብዛኛዋቹ በብጉር ለተጠቁ ሰዋች ይመከራሉ፡፡

በተከሰተዉ ቡግንጅ መልክ፣አይነት እና መጠን በመመርኮዝ ቡግንጅን ለማከም የሚያስችሉ መፍትሆዎች አሉ፡፡

የቡግንጁ አይነት ጥቁር እራስ ያለዉ እና ነጭ ራስ ያለዉ ከሆነ ያለ ሀኪም ማዘዣ በሚገዙ መድሃኒቶች መታከም ይችላሉ፡፡

ነገር ግን የቡግንጁ አይነት ፓፑለስ(ፑስቱለስ) እና ኖዱልስ(ሲይስትስ) ከሆነ የህክምና ባለሙያ ማዘዣ አስፈላጊ ነዉ፡፡

ሁልጊዜም ቢሆን ህመምን ሳይከሰት በፊት መከላከል ይመከራል ሆኖም የህክምናዋቹን አይነት እና ምንነት ማወቅ ቡግንጅ ከተከሰተ በሗላ ለምንወስደዉ እርምጃ ያለዉ ጠቀሜታ እዚህ ግባ የሚባል አይደለም፡፡

ለብጉንጅ ማከሚያነት የሚያገለግሉት መድሀኒቶች ሁለት አይነቶች ናቸዉ፤ያለሀኪም ትዛዝ የሚገኙ እና የሀኪም ፍቃድ የሚያስፈልጋቸዉ ተብለዉ ይከፈላሉ፡፡

ያለሀኪም ትዛዝ የሚገኙ የቡግንጅ መድሃኒቶች

ከታወቁት ያለሀኪም ትዛዝ ከሚገኙ መድሃኒቶች መካከል ቤንዞይል ፐርኦክሳይድ(ሳሊሲይሊክ አሲድ) እና አንተባክቴሪያል ኤጀንቶች የሆኑት እነ ትራይክሎሳን ተጠቃሽ ናቸዉ፡፡

ሁለቱም መድሃኒቶችን በአብዛኛዉ በክሬም እና በጄል መልክ ማግኘት እንችላለን፡፡

እነዚህን መድሃኒቶች ቆዳችን ላይ በመበቀባት የምንጠቀማቸዉ ሲሆኑ የተጎዳ ቆዳን በቀላሉ መላጥ ይችላሉ፡፡

ይህም ባህሪያቸዉ ባክቴሪያን በፍጥነት ከቆዳችን ላይ ለማስወገድ ይረዳል፡፡

እነዚህን መድሃኒቶች ከመጠቀማችን በፊት ቆዳችንን በሞቃት ዉሀ መታጠብና ማድረቅ ያስፈልጋል፡፡

የሀኪም ትዛዝ የሚያስፈልጋቸዉ የቡግንጅ መድሃኒቶች

የከፋ የብጉር ክስተት የሀኪም ትእዛዝ የሚስፈልገዉ መድሃኒት እንደሚያስፈልገን አመላካች ነዉ፡፡

ብጉርን ለማከም ከሚያገለግሉ የሀኪም ትእዛዝ የሚስፈልጋቸዉ መድሃኒቶች መካከል ሬቲኖይድ የሆነዉ አይዞትሬትሪዮን ዋነኛ ተጠቃሽ ነዉ፡፡

የብጉሩ ሁኔታ አስጊ ሲሆን የቆዳ ሀኪሞች የብጉር ህመምን የማከም ብቃት ያለዉን ሬቲኖይድ ማለትም አኩታቴንን እንድንጠቀም ይመክራሉ፡፡

ሆኖም ግን አኩታቴን ከተጠቀምነዉ በሗላ የሚያመጣቸዉ መዘዞች አሉት፡፡ከነዚህም መካከል ትዉከት፣ተቅማጥ እና በሴቶች ላይ የወሊድ ተጽኖን ያሳድራሉ፡፡

ብጉንጅን መከላከያ መንገዶች

ጥሩ የሆነ የግል ንጽህና አጠባበቅ በቆዳችን ላይ ለብጉንጅ መከሰት መንስኤ የሚሆኑትን በካይ ነገሮችን እና በቆዳችን ላይ የሚገኙትን የሞቱ የቆዳ ቅንጣቶችን ቁጥር ለመቀነስ ይረዳናል፡፡

ነገር ግን የግል ንጽህናችንን በአግባቡ ጠብቀንም ቢሆን ብጉንጅን ሙሉ በሙሉ ልንከላከለዉ አይቻለንም፡፡ ብጉንጆች ከጠፋ በሗላ ቀይ ወይም ጥቁር ምልክቶችን በቆዳችን ላይ ጥለዉ ያልፋሉ፡፡

እነዚህ ምልክቶች ይጠፋሉ ፤ሆኖም ግን ቀናት፣ሳምንታት ወይም ወራት ሊፈጅባቸዉ ይችላል፡፡

የጠፋት የቡግንጅ ምልክቶች በቆዳችን ላይ ጉብታ ወይም ስርጉድ ሆነዉ ይታያሉ እሱንም ቢሆን ግን የቆዳ ሀኪም ካማከርን የተወሰኑትን ማጥፋት እንችላለን፡፡

እንግዲህ ስለ ብጉር ይህን ያህል ካልን ሁላችንም የተረዳነዉን በመተግበር ብጉር እንዳይከሰት ከተከሰተም በጊዜ ማከም እንችላለን፡፡

አስተያየትዎን ይፃፉ

በኢትዮጵያ አዲስ ዓለማቀፍ ዲጂታል ቤተ መፃህፍት ሊከፈት ነው

0

አዲሱን ዓለማቀፍ ዲጂታል ቤተ መፃህፍት ለመክፈት ኢትዮጵያ የመጀመሪያዋ አገር ሆና ተመርጣለች፡፡

ቤተ መፃህፍቱ በሰባት የኢትዮጵያ ቋንቋዎች የተዘጋጁ የተለያዩ መፃህፍት እንዲሁም ለእረፍት ጊዜ ንባብ የሚሆኑና በ3 የአፍሪካ ቋንቋዎች የተፃፉ የታሪክ መፃህፍት ይኖሩታል፡፡

ሰባቱ ቋንቋዎች አማርኛ፣ ትግርኛ፣ ኦሮሚኛ፣ ሶማሊኛ፣ ሲዳምኛ፣ ወላይትኛ እና ሀዲይኛ መሆናቸው ታውቋል፡፡

አዲሱ ዲጂታል ቤተ መፃህፍት የዓለማችን ህፃናትና ወጣቶች ለንባብ የሚያስፈልጓቸውን መፃህፍት ለማቅረብ እንደሚሰራ ተገልጿል፡፡

ዓለማቀፍ ትብብር ለመፃህፍት የተሰኘው ጥምረት ደረጃቸውን የጠበቁ የመማርያ መፃህፍትን በማሰባሰብ በዌብሳይትና ተንቀሳቃሽ ስልክ ላይ በዲጂታል እንዲሁም በጥራዝ መልኩ እንዲሰራጩ ይሰራል፡፡

በሂደት መፃህፍትን ከየአካካባቢው ባህል ጋር በማዛመድ ከ300 በላይ በሚሆኑ ዓለማቀፍ ቋንቋዎች የማስተርጎም እቅድ እንዳለም ተገልጿል፡፡

በአሜሪካ፣ ኖርዌይ፣ እንግሊዝና ሌሎች አገራት ድጋፍ የሚንቀሳቀሰው ዓለማቀፉ ጥምረት በኢትዮጵያ የሚከፍተው ይኸው ቤተ መፃህፍት ህፃናትና ወጣቶች ደረጃቸውን የጠበቁ መፃህፍት እንዲያገኙ ያስችላቸዋል ተብሏል፡፡

አስተያየትዎን ይፃፉ